ከሮበርት ጋር ይገናኙ

አባት፣ ባል እና በዋሽንግተን ዲሲ የአምስተኛ ትውልድ አባል እንደሆኔ መጠን ፣ በሕይወት ዘመኔ ከተማችን ስታድግ እና ስትለወጥ ተመልክቻለሁ፡፡ የዲሲ ብሩህ ጊዜያት ከፊታችን እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡

ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳይ

ልጅ በነበርኩ ጊዜ፣ የእኛ ቤተሰብ አባል የሆነበት ማኅበረሰብ በማዲሰን መንገድ፣ በዋርድ 4 ይኖር ነበር፤ የቅዱስ አውጉስቲን ቤተክርስቲያን አባላት የቤተሰባችን አባላት የሆኑ ያህል ነበሩ፡፡

የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ በጡት ካንሰር ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየችኝ፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ደግሞ ከሞት የተረፍኩበት የመኪና አደጋ አጋጠመኝ፤ በዚህ አደጋ የጭንቅላቴ አጥንት ሲሰነጠቅ ከአፌ ውስጥ የተወሰነው ክፍል ደግሞ ወደ ውስጥ ሰረጎደ፡፡ ከአደጋው በማገገም እና በጥልቅ ሃዘን ላይ ሳለሁ፣ የትምህርት ቤት ውጤቴ እጅግ ቀነሰ፤ ይህ ሁሉ ቢደርስብኝም ከቤተሰቤ ጋር ያለኝ ጥብቅ ግንኙነት በመመርኮዝ አሳልፌዋለሁ፡፡ 

ቀጣዮቹን ሰባት ዓመታት በትምህርት ቤት እየወደቅሁ አሳለፍኩ፡፡ ነገር ግን ዕድለኛ ነበርኩ፡- በሕይወቴ ጥቂት በአዋቂነት የዕድሜ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች በእኔ ላይ ያላቸውን እምነት አላጡም፡፡ በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ከዲሲ የማኅበረሰብ አባላት ያገኘሁትን ድጋፍ ባላገኝ ኖሮ፣ በእርግጠኝነት ዛሬ እዚሀ አልገኝም ነበር፡፡

ምኞቴን ማግኘት

በአፍላ የወጣትነት ዘመኔ ያለፍኩባቸው ውጣ ውረዶች ችግሮችን እና እንቅፋቶችን በጥንካሬ፣ በትዕግስት እና በኃላፊነት ስሜት እንድጋፈጥ ትምህርት ሰጥተውኛል፡፡ በጥንካሬ እና በትጋት ችግሮቼን ለማለፍ ችያለሁ፤ ከአርክቢሾፕ ካሮል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከሜሪላንድ ሴንት ሜሪ ኮሌጅ እና ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የዋሽንግተን የሕግ ኮሌጅ ለመመረቅ በቅቻለሁ፡፡ 

ከሕግ ትምህርት ቤት በኋላ ደግሞ፣ ሕይወቴን ላሳደገኝ ማኅበረሰብ መልሼ በመስጠት ለማሳለፍ ወስኛለሁ፡፡ በሞንትጎምሬ ካውንቲ፣ የሜሪላንድ ዲስትሪክት ፍርድ ቤት የሕግ ሬጅስትራር በመሆን ሰርቻለሁ፤ ከዚያ በማስከተል ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮንግረስ አባል ለነበሩት ኤለኖር ሆልምስ ኖርተን ለአምስት ዓመታት የሕግ ማርቀቅ አማካሪ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ በዚህ ሥራዬ ኮንግረሱ በዲሲ ላይ የነበረውን የተቆጣጣሪነት ሥልጣን ለማላላት እና ዲሲ ራሷን የቻለች ከፍለ ግዛት እንድትሆን ታግያሁ፡፡

ለኮንግረስ አባል ኖርተን በመስራት ላይ ሳለሁ፣ ከዙሪያዬ ከተማችን እየተቀየረች እንደመጣች ለማየት ችያለሁ፡፡ እንደ ሌሎች በርካታ ቤተሰቦች ሁሉ፣ የቤተሰብ መፈናቀል በቀስታ እና በሂደት አጋጥሞኛል፡፡ አመራሩ አሁን በከተማችን ካሉት ይልቅ ባለጠጎች ወደ ከተማችን እንዲመጡ ቅድሚያ ሲሰጥ በተግባር ተመልክቻለሁ፡፡ ከተማችን በይበልጥ ለነዋሪዎቻችን እንድትሰራ ለማድረግ በሕግ ትምህርት ቤት እና በምክር ቤቱ ስሰራ ያገኟቸውን ክህሎቶቼን መጠቀም እንዳለብኝ ወስኛለሁ፡፡ 

በ2014፣ ማኅበረሰብን በማድመጥ እና በሁሉ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ነዋሪዎች የሚሰጡ ድጋፎችን በማስፋት ላይ በማተኮር ማኅበረሰቡ ከዲሲ የዋና ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ጋር በትብብር እንዲሰራ የሚያስችል ብሉፕሪንት ለመንደፍ እና ተፈጻሚ ለማድረግ ከዋና ዓቃቤ ሕግ ካርል ራሲን ጋር መስራት ጀመርኩ፡፡

ወደ ፊት ማማተር 

በመጀመሪያ ለዲሲ ምክር ቤት የተወዳደርኩት በ2014 ነበር፤ ማሸነፍ አልቻልኩም እንጂ አልተሸነፍኩም፡፡ በ2016 ደግሞ በድጋሚ ተወዳድሬ አሸነፍኩ፡፡ በሕይወቴ እጅግ ከፍ ያለ ክብር ከምሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የዲሲ ምክር ቤት አባል ሆኜ መስራቴ ነበር፡፡

በምክር ቤቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ልናሳካቸው በቻልናቸው ሁሉ ከፍ ያለ ኩራት ይሰማኛል፡፡ የሕጻንነት ዘመን ትምህርትን ለማስፋፋት የሚያስችለን ሕግ ያጸደቅን ሲሆን፣ ሕጉ አዲስ ብሔራዊ ስታንዳርድ ለማስቀመጥ አስችሎናል፡፡ እስረኛ ነዋሪዎች የመምረጥ መብታቸውን መልሰው እንዲጎናጸፉ በአገሪቱ የመጀመሪያ ሕግ እንዲወጣ አድርጌያለሁ፤ እስረኛ ነዋሪዎች በጂም ክሮው ፖሊሲዎች ምክንያት የመምረጥ መብታቸው ተገፎ ነበር፡፡ ለቅጥር ከፍተኛ እክሎች ላሉባቸው ሰዎች የሥራ ኃይል ፕሮግራሞችን ለማስፋት ታግያለሁ፣ ወንድሜ ተመላሽ ዜጋ እንደመሆኑ መጠን ከእርሱ ተሞክሮ በመውሰድ ለተመላሽ ዜጎች እገዛ የሚያደርገውን ኤጀንሲ መጠን በእጥፍ ለማሳደግ ሰርቻለሁ፡፡ 

ወደ ፊት መመልከት

የዲሲን የወደፊት ሁኔታ አካታች እና ፍትሐዊ ለመድረግ ከንቲባ ያስፈልገናል፡፡ ከተማዬን፣ ቤቴን ለማገልገል በመወዳደር ላይ ነኝ፡፡ በአንድነት ለሁላችንም የምትሰራ ዲሲ መፍጠር እንደምንችል አምናለሁ፡፡ የእኛን እንቅስቃሴ እንደሚቀላቀሉ አምናለሁ፡፡